top of page

የቆጠር ገድራ የተፈጥሮ ደን የት እንደሚገኝ ያውቁታል? ቦታው በእዣ ወረዳ በጉራጌ ዞን ከሚገኙ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች መገኛ ከሆኑ አካባቢዎች ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሰፋፊ የተፈጥሮ ደኖች ልዩ ቦታ አላቸው። የቆጠር-ገድራ የተፈጥሮ ደን በወረዳው ልዩ ስሙ #ቆጠር_ገድራ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሚገኝ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን ነው:: አካባቢውና ደኑ ስያሜያቸውን ያገኙት በአከባቢው ከሚኖረው ጎሳ (“ጥብ”) መጠሪያ (“ቊጠር”) እና በወቅቱ አከባቢውን ሸፍኖ ከነበረው በአካባቢው አጠራር “ገድራ” (አስታ) ከተሰኘ ቁጥቋጦ ነው፡፡ “ቊጠር” እና “ገድራ” ተጣምረው “ቊጠር-ገድራ” የሚለውን ስያሜ አስገኝተዋል፡፡ “ቊጠር” አሁንም በብዛት በአካባቢው ሰፍሮ የሚኖር “ጥብ” ነው፡፡


በዚህም አካባቢው “የቊጠር አፈር” (የቊጠር መሬት/ምድር/መኖሪያ/ርስት) በሚል ይታወቃል፡፡ “ገድራ” ግን በአሁኑ ወቅት ጠፍቷል በሚባል ደረጃ እምብዛም አይታይም፡፡ “ገድራ” በቀደመው ዘመን በተለይ በማይታረስ መሬት ላይ በስፋት ይገኝ እንደነበረና በሂደት በጥድና በሌሎች ዛፎች ተሸንፎ ሊጠፋ እንደቻለ ከደኑ ታሪክ ጋር ተያይዞ ይነገራል፡፡ በደኑ ዙርያ ባሉ አካባቢዎች የእርሻ መስፋፋትም ለቁጥቋጦው መጥፋት አስተዋጽኦ እንዳለው ይጠቀሳል፡፡


በዚህ ሁኔታ የደኑ መነሻ ከጥንት ጀምሮ በአካባቢው ሰፍሮ በሚኖር ጎሳ (“ቊጠር ጥብ”) ተከብሮ ይጠበቅ ስለነበረ ከ“ገድራ” በተጨማሪ የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎች እየበቀሉና እየተስፋፉ በመቀጠል በሂደት በብዛት በሀበሻ #ጥድ እየተሸፈነ ሊመጣ እንደቻለ ይነገራል፡፡ ከጥድ በተጨማሪ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችም ይገኙበታል። የደኑ ጠቅላላ ይዞታ/ስፋት በትክክል ባይታወቅም ከ320 – 350 ሄክታር ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡


ደኑ ችፍግ/ጥቅጥቅ ብሎ በመብቀል ከሩቅ ለሚመለከተው በባለሙያ የተከረከመ እስከሚመስል ድረስ ተፈጥሮ ራሱ ከርክሞ ለአከባቢው ልዩ ውበትና ግርማ ሞገስ አላብሶት ይገኛል፡፡ ደኑ ከማንኛውም ዓይነት ንክኪ ነጻ ሆኖ ኅብረተሰቡ በአካባቢው ባህል መሠረት ጥበቃና እንክብካቤ ያደርግለታል፡፡ ከደኑ ዛፍ መቁረጥ ቀርቶ የወደቀውን ዛፍ እንኳ ያለ #ባህላዊ ሸንጎ (ሽማግሌዎች) እውቅናና ይሁንታ ማንሳት አይቻልም፡፡


በመሀላ የታሰረ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ከውስጥም ሆነ ከውጪ #ደን ጨፍጫፊዎች እየተከላከለውና እየጠበቀው ይገኛል፡፡ ሆኖም ለአካባቢያዊና ማኅበረሰባዊ አገልግሎት (ለምሳሌ፡- ለት/ቤት ግንባታ፣ ለመንገድ ሥራ፣ ወዘተ.) ሲፈለግ በባህላዊ ሥርዓት መሠረት መሀላው በሽማግሌዎች እንዲነሳ ይደረግና ይፈቀዳል፤ ከዚያም ወዲያውኑ መሀላው እንዲጸና ይደረጋል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ባህላዊ ሥርዓት ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬ ላይ ደርሷል፤ ይህ ሥርዓት እንዲቀጥል የቀጣዩ ትውልድ አደራ ይሆናል፡፡


ደኑ በዚህ ጊዜ ነበር ለማለት ጥናትና ምርምር የሚጋብዝ ቢሆንም እድሜ-ጠገብ እንደሆነ ግን ለሚያየው ሁሉ ለመገመት የሚያዳግት አይሆንም፡፡ ደኑ በዘመናት እድሜው ተመንጥሮ የእርሻ መሬት ያልሆነበት ዋና ምክንያት ቀደምቱ የደኑ ባለቤቶች በነበራቸው የሰው፣ የእንስሳት፣ የአራዊትና እንዲሁም የቁስ አካላት ሥርዓታዊ አስተዳደራዊ ደንብ መሠረት ነው፡፡


የጥንቱ ሥርዓት ከትውልድ ትውልድ በቅብብሎሽ አሁንም ድረስ ተግባር ላይ ያለና በአካባቢው ነዋሪ አዕምሮ ታትሞ የሚኖር ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ደኑን እንደ መጠሪያው ወይም ስምና ምልክት አድርጎ ስለሚረዳው፣ አልፎ ተርፎም ታሪክና ማንነት ነው ብሎ ስለሚያምን የወለደው ልጅ እንኳ በታቃራኒ ቆሞ ቢያገኘው አሳልፎ ከመስጠት ወደ ኋላ አይልም፤ “በቆጠር-ገድራ የመጣ በዓይኔ መጣ” ይላል፡፡


ደኑ በማኅበረሰብ ተሳትፎ ለረጀም ጊዜ ተጠብቆ የቆየ ስለሆነ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ ከመቆየቱም በላይ ስፋቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚመጣ ይጠበቃል፡፡ ምክንቱም በደኑ ውስጥ የሚወድቁ ፍሬዎች እዚያው እየበቀሉ አልፎ አልፎም ከደኑ መሬት ይዞታ ውጭ የሚበቅልበት ሁኔታ ስለሚኖርና ምንም ዓይነት የደን ቆረጣና ጭፍጫፋ ስለማይካሄድ የደኑ መስፋፋት ይጠበቃል፡፡


በሀገራችን ያሉ ደኖች የእርሻ መሬት ፍለጋ እየወደሙ ባለበት ሁኔታ ቆጠር-ገድራ የተፈጥሮ ደን በዚህ ልክ ሳይቀንስ እንዲያውም ለሌሎች ምሳሌ በሚሆን መልኩ ስፋቱ በመጨመር በማኅበረሰቡ ተጠብቆ መቆየቱ እጅግ የሚያስገርምና ለሌሎች ደን አልሚዎች ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡


የቆጠር-ገድራ የተፈጥሮ ደን መኖር አካባቢውና ዙርያ-ገቡ የሚታዩና የማይታዩ ገጸበረከቶች አድሎታል፡፡ የወል ሀብት በመሆኑ በይዞታው የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ማቋቋም አስችሏል፡፡ ቆጠር-ገድራ ት/ቤት፣ ቆጠር-ገድራ መስጅድ፣ ቆጠር-ገድራ ጤና ጣቢያ፣ ቆጠር-ገድራ ኪዳነምህረት ገዳም፣ እና ሌሎችም የሚታዩ ሀብቶች ናቸው፡፡ ከማይታዩ የደኑ ጸጋዎች መካከል ደግሞ በተለይ የሥነ-ምህዳር አገልግሎት ተብሎ የሚታወቀው አንዱ ነው፡፡


የሥነ-ምህዳር አገልግሎት በምድር ላይ ሕይወት እንዲቀጥል ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል። ይህ አገልግሎት በሰው ልጅና በተፈጥሮ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሳቢያ ተጽዕኖ እየተደረሰበት ቢሆንም ማኅበረሰቡ የራሱ የሆነ የተፈጥሮ አጠባበቅ ዘዴ ስላለው የሥነ-ምህዳር አገልግሎት ባለበት አገልግሎት እየሰጠ ሊቆይ የሚችልበት እድል አለ።


የሥነ-ምህዳር አገልግሎቶች በአብዛኛው በዓይናችን ስለማናያቸው ቀጥታ ከገበያ እንደምንገዛው እቃ ዋጋ ማውጣት የተለመደ አይደለም። የሥነ-ምህዳር አገልግሎቶች ወይም የተፈጥሮ ሀብቱ ዋጋ እንዳለው ወይም ገንዘብ እንደሚያወጣ ካላወቅን ደግሞ ለመንከባከብም ሆነ ለመጠበቅ መነሳሳት አይኖርም። በሕይወታችን ሙሉ የምንጠቀማቸውና ከተፈጥሮ ሀብት የምናገኛቸው የሥነ-ምህዳር አገልግሎቶች በዓይናችን የማናያቸው ቢሆንም ዋጋቸው ብዙ ነው፡፡ አሁን አሁን በገንዘብ መተመንም ተችሏል፡፡


ቆጠር-ገድራ የተፈጥሮ ደን የሚሰጣቸው የስነ-ምህዳር አገልግሎቶች በርካታ ናቸው፡፡ ከደኑ የሚገኙ ፍራፍሬዎች፣ የእንስሳት መኖና ጥላ አገልግሎት፣ የአየር ንብረት እንዳይዛባ መከላከል፣ የማኅብረሰቡ ማኅበራዊ ትስስር እንዲጠናከር ማድርግ፣ በርካታ የውሀ ምንጮች፣ የመሬት ለምነት መጠበቅ፣ ለብዝሀ ህይወት ምቹ አካባቢዊ ሁኔታ መፈጠር፣ ንብ ለማነብ፣ ከጎርፍ ለመከላከል፣ ለባህል ህክምና የሚያገለግሉ እፅዋት መኖር፣ ወዘተ. መጥቀስ ይቻላል፡፡ ደኑ በውስጡ ብዙ የዕፅዋት ዝርያ ከመያዙም ባሻገር ከስነ-ምህዳር አገልግሎቶች ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር በጣም ከፍተኛ ነው፡፡


በደኑ ዙሪያ በርካታ የውሃ ምንጮች መኖራችው የደኑ መኖር ካበረከታቸው ገፀ-በረከቶች አንዱ ነው፡፡ ከደኑ በታችኛው ተፋሰስ ሁለት የውሃ ፋብሪካዎች መኖራቸው ለዚህ አንዱ ማሳያ የሚሆን ነው፡፡ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞችና ምንጮች መኖራቸውና የከርሰምድር ውሃ በቀላል ቁፋሮ ማግኘት መቻል የደኑ አዎንታዊ ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው፡፡


በደኑ ውስጥም ሆነ በዙሪያው የአፈር መሸርሸር አለመታየቱ ደኑ ካበረከተልን ፀጋዎች አንዱ ነው፡፡ ቆጠር-ገድራ ደን ብዙ የብዝኃ ህይወት ባለቤት እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ እድሜ ጠገብ ዛፎች፣ የተለያዩ የእፅዋት ዝርያዎች፣ የአዕዋፋት ዝማሬዎች፣ የዱር እንስሳት መኖራቸው ልዩ ከሚያደርጉት የተፈጥሮ ደኖች አንዱ ነው፡፡ ደኑን በማኅበረሰብ ተሳትፎ ተጠብቆ የቆየ ስለሆነ እነዚህ ብዝኃ ህይወት ለመኖሪያነት ምቹ ሆኗቸዋል፡፡


ዛሬ ባደጉ ሀገሮች ከፋብሪካ በሚመነጭ በካይ ጋዝ አማካይነት የአየር ብክለት በእጅጉ ከመጨመሩ የተነሳ የዓለም ሙቀት መጨመር፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የዝናብ ማጠርና መብዛት፣ ሌሎችም የተፈጥሮ አደጋዎቸ እየተከሰቱ ስለሆነ የሰው ልጅ ህይወት ፈተና ላይ ወድቋል፡፡ በካይ ጋዝ ለመቀነስ አረንጓዴ ተክሎች ማብዛትና መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡


ይህን በካይ ጋዝ የሚመጥ አረንጓዴ ተክሎች በብዛት ባላደጉ ሀገሮች ስለሚገኝ ያደጉ ሀገሮች ከኢንዲስትሪያቸው በሚያመነጩት በካይ ጋዝ ልክ ማካካሻ ገንዘብ በፍቃደኝነትና በግዴታ በካርበን ሽይጭ ህግ መሠረት መክፍል አለባቸው የሚል ዓለም አቀፍ ስመምነት አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ቆጠር-ገድራ የተፈጥሮ ደን በርካታ ረጃጅም ዛፎች ስላሉት በቁመታቸውና በውፍረታቸው መጠን ከካርበን ሽያጭ ገንዘብ ማግኘት የሚችልበት እድል ይኖራል፡፡


አንድ ቶን ካርበን ከ20-120 ዶላር በሄክታር ዋጋ እንደሚያወጣ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ቆጠር-ገድራ ደን የካርበን ሽያጭ ገበያ ቢቀላቀልና በሄክታር 40 ዶላር እንኳ ቢሸጥ በዓመት እስከ 14 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሊያስገኝ ይችላል፡፡ ከዚህም በላይ ከደኑ የምናገኛቸው ሌሎች የስነ-ምህዳር አገልግሎቶች እያንዳንዳቸው ወደ ገንዘብ ቢቀየሩ ከግብርና መሬት በዓመት ከሚገኘው በላይ ከደኑ የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡


በመጨረሻም አካባቢዊ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳው በመረዳት ደኑን በመጠበቅና በማስተዋወቅ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡ በተለይ የዘርፉ ተመራማሪዎች ጥናትና ምርምር በማድረግ (ይዞታ/ሽፋን፣ እድሜው፣ እጽዋት ዝርያ፣ ወዘተ.) እና የጥናቱ ውጤቶች በማሳተም ለዓለም-አቀፉ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ፣ ሣይንሳዊ ዘላቂ የደን አስተዳደር ሥርዓት በማስተዋወቅ የዘላቂነት ስጋት እንዲቀንስ ማድረግ፣ የካርበን ሽያጭ ገበያ እንዲቀላቀል በማድረግ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማመቻቸት፣ ወዘተ. ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆን ይኖርበታል፡፡


በተጨማሪም በማኅበረሰቡ ዘንድ የዳበረው ለተፈጥሮና ለተፈጥሮ ጥበቃ ያለው አስተሳሰብ ጥልቅ ስለሆነ ማኅበረሰቡ ደኑን ለማቆየት የተጠቀመበት ማኅበራዊ እሴቱ ተጨማሪ ምርምር የሚጋብዝና እንደ መልካም ተሞክሮ ተወስዶ ለሌሎችም አካባቢዎች እንዲደርስ ቢደረግ ከደን/አካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ አገራዊ ፋይዳው ቀላል አይሆንም፡፡ ይህም ደኑን ዘላቂ በሆነ መልኩ ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ይረዳል፡፡



ቆጠር-ገድራ ት/ቤት፣ ቆጠር-ገድራ መስጅድ፣ ቆጠር-ገድራ ጤና ጣቢያ፣ ቆጠር-ገድራ ኪዳነምህረት ገዳም፣ እና ሌሎችም የሚታዩ ሀብቶች ናቸው









ቆጠር-ገድራ ደን የካርበን ሽያጭ ገበያ ቢቀላቀልና በሄክታር 40 ዶላር እንኳ ቢሸጥ በዓመት እስከ 14 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሊያስገኝ ይችላል፡፡

21 views0 comments

The Gurage people have a rich and diverse cultural heritage, which is reflected in their customs, traditions, and way of life. Some of the key aspects of Gurage customs include:-

1. Social Structure: The Gurage society is traditionally organized into a hierarchical social structure with distinct age sets or groups, each with its responsibilities and roles within the community.

2. Religion: Most Gurage people practice Christianity, with Orthodox Christianity being the predominant faith, while Islam is the second major faith in Gurage. Traditional religious beliefs and practices also play a significant role in their culture.

3. Cuisine: The Gurage are known for their unique culinary traditions, including dishes such as kitfo (minced raw meat), tibs (grilled meat), injera (a sourdough flatbread), and various spicy stews made from lentils or vegetables.

4. Music and Dance: Music and dance are integral to Gurage culture. Traditional musical instruments like the kebero (drum), masinqo (a single-stringed fiddle), andir, dibea, turumbia are often used during festive occasions or ceremonies.

5. Clothing: Traditional attire for both men and women includes brightly colored woven garments made from cotton or other natural fibers, often adorned with intricate patterns and designs specific to Gurage culture.

6. Marriage Customs: Marriage among the Gurage involves various rituals, negotiations between families, as well as traditional ceremonies that celebrate the union of the couple.

7. Rituals and Ceremonies: The Gurage people have several rituals and ceremonies including fejet, kertha, nebuar, chishet (mainly in Cheha), mewulid, and so on. cheha), mewulid and so on..

21 views0 comments
1
2
bottom of page